ፈዷኢል አል-አዕማል

5.00 $

ነብያችን ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ.) በዚህም ሆነ በመጨረሻው ዓለም በሚጠቅሙን በበርካታ መልካም ሥራዎች አመላክተዉናል፤ አነሳስተዉናል፡፡ በርካታ ዑለሞች እነኚህኑ ምልከታዎች በተለያየ መልኩ በመጽሐፍ መልክ ለማዘጋጀት ሞክረዋል፡፡ ይህ መጽሐፍም ከነብዩ (ሰ.ዐ.ወ.) ሐዲሦች የተውጣጡ በላጭና መልካም የሆኑ ሥራዎችና ታሪኮች ዉብ በሆነ መልኩ የተቃኙበት ነው፡፡ መጽሐፉ የነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ.) ባልደረቦች ዓለማዊ ሕይወት ምንነት፣ ለዕውቀት የነበራቸዉን ትጋትና ጉጉት፣ ጀግንነታቸዉን፣ ለሶላት የነበራቸዉን ፍቅር እንዲሁም ለነብያቸው ያሳዩት የነበረው ዉዴታ ተዳሶበታል፡፡ ታሪካቸው መንገዳቸዉን እንድንከተል የሚያነሳሳ እና የሚስብ ነው፡፡ መጽሐፉ 12 ምዕራፎች አሉት፡፡

አዘጋጅ ፡ መውላና ሙሐመድ ዘከርያ
ትርጉም ፡ ዶ/ር ኢድሪስ ሙሐመድ
የገጽ ብዛት ፡ 209
የታተመበት ዓመት ፡ 1992
ከመጽሐፉ ፡
ሑዘይፋ (ረ.ዐ) ከዕውቅ ሶሓባዎች ውስጥ አንዱ ነው፡፡ የነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ.) ምስጢር ጠባቂ በመባል ይታወቃል፡፡ የመናፍቃንን ስም ዝርዝር ገልጸውለታል፡፡ ሙስሊሙን የሚገጥሙትን ፈታኝ ክስተቶችም አሳውቀውታል፡፡ ሑዘይፋ (ረ.ዐ) እንዲህ ብሏል፡- ሌሎች ሰዎች የአላህ መልዕክተኛን (ሰ.ዐ.ወ.) ስለ ጥሩ ነገሮች ይጠይቁ ነበር እኔ ደግሞ ስለ አዋኪ (መጥፎ) ክስተቶች እጠይቅ ነበር- ከነርሱ መጥጠበቅ እችል ዘንድ፡፡’’
ሑዘይፋ (ረ.ዐ) ፊትና’’ን በተመለከተ የሚከተለውንና ከነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ.) ጋር ያደረገውን ቃለ-ምልልስ ገልጾልናል፡-
ሑዘይፋ፡- የአላህ መልዕክተኛ ሆይ! እርስዎ ካጐናጸፉን መልካም የሕይወት ገጽታ በኋላ ወደ መጥፎ ገጽታ እንመለስ ይሆን?
ነቢዩ፡- አዎ! መጥፎ (እኩይ) ክስተት እውን ይሆናል፡፡
ሑዘይፋ፡- ከዚያ እኩይ ገጽታ በኋላ መልካም ነገር ይመጣ ይሆን?
ነቢዩ፡- ሑዘይፋ! ይልቅ ሂድና ቁርኣንን አንብብ፡፡ ትርጉሙን አስተንትን ትዕዛዛቱንም ተከተል፡፡
የሑዘይፋ (ረ.ዐ) ጭንቅ ግን ይበልጥ ጨመረ፡፡ በሙስሊሞች ላይ ወደፊት ስለሚደርሰው የፊትና ዘመንም ይበልጥ ጠየቃቸው፡፡
ሑዘይፋ፡- የአላህ ነቢይ ሆይ! ከዚያ የፈተናና ቀውጢ ጊዜ በኋላ መልካም ጊዜ ይመጣ ይሆን?
ነቢዩ፡- አዎ! መልካም ጊዜ ይመጣል ግና የሰዎች ቀልብ እንደ ድሮው አይሆንም፡፡
ሑዘይፋ፡- ከዚህ መልካም ሁናቴ በኋላ እኩይ ክስተት ይስተዋል ይሆን?
ነቢዩ፡- አዎ ሰዎችን ወደ ሲኦል የሚነዱ አሳሳች ግለሰቦች ይመጣሉ፡፡
ሑዘይፋ፡- ይህን ጊዜ ቢያጋጥመኝ ምን ማድረግ ይኖርብኛል;
ነቢዩ፡- በአንድ መሪ ሥር የተባበሩ ሙስሊሞች ካገኘህ ከነርሱ ጋር ተባብረህ ሥራ፡፡ ካልሆነ ግን ከማንኛውም አንጃ ራስህን አግልል፤ ወይም ጫካ ግባ -እስክትሞት ድረስ፡፡’’
ሑዘይፋ (ረ.ዐ) ጣዕረ-ሞት ውስጥ በገባበት ወቅት ከፍተኛ ጭንቀት ተነበበበት አለቀሰም፡፡ ሰዎችም እንዲህ አሉት፡-ከዚህ ዓለም በመለየትህ ነው የምታለቅሰው?’’ ሲሉ ጠየቁት፡፡ “የለም ይህማ አያስለቅሰኝም፡፡ ሞትን አፈቅራለሁ፡፡ የማለቅሰው ከዚህ ዓለም በምለይበት ወቅት አላህ በኔ (ሥራ) ይደሰት ወይስ አይደሰት የማውቀው ነገር ባለመኖሩ ነው፡፡’’
ከዚያም እንዲህ በማለት ዱዓ አደረገ፡- “አላህ ሆይ! የሕይወቴ የመጨረሻ ወቅት ይህ ነው፡፡ ምን ጊዜም እንደምወድህ ታውቃለህ ካንተ ጋር መገናኘቴ ብሩክ ይሆን ዘንድ እማጸንሃለሁ፡፡’’

አሳታሚ ፡ ነጃሺ ማተሚያ ቤት

Category: